- Sat, 11/24/2012 - 13:26
- 0 Comments
አዲስ አበባ በሚካሄደው የባቡር መስመር ግንባታ ምክንያት የአቡነ ጴጥሮስና የዳግማዊ ምኒልክ ሃውልት ይፈርሳል በሚል የሚነዛው ወሬ ከእውነት የራቀ ነው አለ የኢትየጵያ ምድር ባቡር ኮረፖሬሸን።
በግንባታው ምክንያት የአቡነ ጴጥሮስ ሃውልት ለደህንነቱ ሲባል ለጊዜው እንዲነሳ የሚደረግ ሲሆን በቅርቡ በነበረበት ስፍራ መልሶ ይተከላል ብሏል። የምኒልክ ሃውልትን ግን ግንባታው ጭራሽኑ አይነካውም ነው ያለው ኮርፖሬሽኑ።
የአዲስ አበባ ከተማን የትራስፖርት ችግር ለማስተካከል የባቡር መስመር ፕሮጀክት ግንባታ እየተካሄደ ነው።
የባቡር ግንባታው ከሚከናወንባቸው አንዱ በሆነው ፒያሳ ጊዮርጊስ አካባቢም ከግንባታው በተቀራኒው የሆነ ሀሳብ ሲነገር እየተሰማ ሲሆን ፥ በተለይ የማህበረሰብ ድህረ ገፆችና የተለያዩ አካላት የአቡነ ጴጥሮስና የሚኒልክ ሀውልት በባቡር መስመር ግንባታው ምክንያት ሊፈርሱ ነው በሚል ሰፊ ዘመቻ እየተካሄደ ነው።
በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሆኑትን አቶ አበበ ፥ በአካባቢው አሁን እየተከናወነ ያለው ስራ በእቅዱ መሰረት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው ፥ የአቡነ ጵጥሮስ ሀውልት ይፈርሳል የሚለው ፍፁም ስህተትና ተራ ወሬ ነው ብለዋል።
ሀውልቱ ምንም ችግር ሳይደርስ የባቡር መስመር ዝርጋታው ይከናወናል ያሉት ሃለፊው ፥ የባቡር መተላለፊያ ዋሻ ከሃውልቱ ስር ስለሚገነባ ፤ ግንባታው እስኪያልቅ ድረስ ሃውልቱ ለጥቂት ጊዜ ተነስቶ ከዋሻው መጠናቀቅ በኋላ ወደ ቦታው እነደሚመለስ ተናግረዋል።
አያይዘውም ይህ የባቡር መስመር ግንባታ የዳግማዊ ሚኒሊክ ሀውልትን በምንም መልኩ እንደማይነካው የሚወራው ወሬ መሰረተ ቢስ መሆኑንም ነው ያስረዱት።
የባቡር መስመር ግንባታው በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን እና ስራው ፥ ከአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ፣ ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ከአዲስ አበባ ውበትና ጽዳት ኤጀንሲና ከሌሎችም ጋር በትብብር ነው የሚሰራው ብለዋል አቶ አበበ።
የክትትል ስራውም በጋራ እንደሚከናወን ጠቅሰው ስራው አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ በመከናወን ላይ ነው ማለታቸውንም ብርሃኑ ወልደሰማያት ዘግቧል።
From Fana Broadcasting
- 323 reads
Post new comment