- Mon, 08/27/2012 - 22:54
- 0 Comments
Alemneh Moges
ወርቅ በእሳት ይፈተናል፡፡ በእሳት የሚፈተነው ግን የወርቅ ማዕድን ብቻ አይደለም፡፡ ወርቅ ሕዝብ ጭምር እንጂ፡፡ ወርቅ ሕዝብ፣ ጨዋ ሕዝብ፣ አስተዋይ ሕዝብ፣ ቅንና አገር ወዳድ ሕዝብ በችግርና በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ይፈተናል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰሞኑን ተፈትኗል፡፡ እየተፈተነም ነው፡፡ በሚያኮራ፣ በሚያስመካና በሚያስገርም ሁኔታ ፈተናውን በድል እየተወጣ ነው፡፡ አኩሪ፣ የሚያስመካ፣ ቅን፣ ሀቀኛ፣ ባህሉንና ታሪኩን እያስመሰከረና እያጠናከረ የሚኖር ሕዝብ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ በእሳት ቢፈተንም ምንጊዜም ወርቅ ሕዝብ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር አሳይቷል፡፡ አስመስክሯል፡፡
ፈተናው የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባልተጠበቀ ሁኔታና ወቅት ከዚህ ዓለም በሞት መለየትና ለሕዝብ በድንገትና ባልተጠበቀ ሁኔታ ይፋ መሆኑ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ጠላቶችና በጠላት አገልጋዮች ሲነገር፣ ሲተነበይና ስለት ሲገባለት የነበረው የጠቅላይ ሚኒስትር ሞት ሲሰማ ሕዝብ እርስ በርሱ ይባላል፣ ይተራረዳል፣ ይታኮሳል፣ ይፋጃል ኢትዮጵያም ያበቃላታል የሚል ነበር፡፡
ሠራዊቱና ፖሊስም እርስ በራሱ ይዋጋል፣ የኢሕአዴግ የፖለቲካ ድርጅቶችም ይከፋፈላሉ፣ ይተራረዳሉ የሚል ትንበያ ነበር፡፡ እኔ ሥልጣን ልያዝ እኔ ጠቅላይ ሚኒስትር ልሁን እየተባባሉ ይጣላሉ፣ ኢሕአዴግም ያበቃለታል የሚል ነበር ከጠላትና ከጠላት አገልጋዮች ሲጐሰም የነበረው ነጋሪት፡፡
የተባለው አልሆነም፤ የተተነበየው አልደረሰም፤ የፈሰሰው የጠላት ገንዘብ ውጤት አላስገኘም፡፡
እንኳን ሊበታተን፣ ሊናከስ፣ ሊባላና ሊተራረድ በተቃራኒው የኢትዮጵያ ሕዝብ መቀራረብ፣ በጋራ ማዘን፣ ማልቀስና ለፈጣሪ ኢትዮጵያን ጠብቃት ብሎ መፀለዩ ነው ጐልቶ የታየው፡፡
በዘር ሳይለያይ፣ በሃይማኖት ሳይለያይ፣ በዕድሜ ሳይለያይ፣ በፆታ ሳይለያይ፣ ሁሉም ዜጋ በየመሥርያ ቤቱም፣ በየቤቱም፣ በየካፌና ሬስቶራንቱም፣ በየሱቁ፣ በየመንገዱ፣ በየታክሲው፣ በየአውቶብሱ ሁሉም ያዝን ነበር፡፡ ሁሉም ስለአገሩ ያስብ ነበር፡፡ ሁሉም ስለሞተው መሪው በበጐ ይነጋገራል፡፡ ልዩ ትዕይንት ነበር፡፡ በኢትዮጵያዊነት የሚያስኮራ አኩሪና አስመኪ ትዕይንት፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሐዘኑን ለመግለጽ ወደ መገናኛ ብዙኅን ጐረፈ፡፡ ሁሉም በየከተማው ሐሳቡን ለመግለጽ መሰባሰብ ጀመረ፡፡ የለቅሶ ቦታ አለ ወደተባለበት ጐረፈ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አስከሬን ምሽት ላይ ይገባል መባሉን ሲሰማ ሕዝብ ወደ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ጐረፈ፣ ተሰባሰበ፣ ተላቀሰ፣ የሕዝብ መሰባሰብና መላቀስን ማየት ራሱ ስሜትን የሚነካና የሚያስለቅስ ነበር፡፡
ደሃዎች ነበሩ፤ ሀብታሞች ነበሩ፤ ወጣቶች ነበሩ፤ ሽማግሌዎች ነበሩ፤ አሮጊቶችም ነበሩ፡፡ ተራ ሰው ነበረ፤ ባለሥልጣን ነበረ፤ ሲቪል ነበረ፤ ፖሊስ ነበረ፤ ከሁሉም ብሔር ብሔረሰብ ነበረ፤ ከሁሉም ሃይማኖት ነበረ፤ ሁሉም በጋራ ሐዘኑን ይገልጽና ያለቅስ ነበረ፡፡ ለማመን የሚያቅት ሐዘን ነበር፡፡ እስከ ሌሊቱ ስምንት ሰዓት ድረስ መንገድ ላይ ሕዝብ ነበር፡፡
በሌላ ጊዜ ሦስት ደቂቃ ብቻ ይወስድ የነበረው ከቦሌ ቤተ መንግሥት መንገድ፣ አስከሬኑ የገባ ዕለት ግን ቤተ መንግሥት ለመድረስ ሦስት ሰዓት ፈጀ፡፡ በየመንገዱ ሕዝቡ እየተላቀሰ፣ የአስከሬን ተሽከርካሪውን ልንካ እያለና የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ቤተሰብን እያየሁ ላጽናና በማለት እየተላቀሰና እየተቃቀፈ ታየ፡፡
ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ለሕዝብ ክፍት ነበር፡፡ ያለ ፍተሻ! ቤተ መንግሥት ለሕዝብ ክፍት ሆነ፤ ያለ ፍተሻ፡፡ ሕዝቡ ወደ ቤተ መንግሥትም ጐረፈ፡፡ በአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ሠልፍና ወረፋ ያዘ፡፡ ረብሻ የለ፣ ሽብር የለ፣ በሥነ ሥርዓት እየተሰባሰበ ገባ ወጣ በማለት አለቀሰ ተላቀሰ፡፡ አስከሬኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ውስጥ ስለተቀመጠ ቤተ መንግሥት የገባው ሕዝብ፣ ትልቅና የተለየ ሕንፃ አያለሁ ብሎ የጠበቀ ሕዝብ ተራ፣ ትንሽና ጠባብ ቢሮ ሲያይና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ይህ ነበር መባሉን ሲሰማ አዘነ፡፡ እዚህች ክፍል ውስጥ ሆነው ነው ይህን ሁሉ ሥራ ሲሠሩ የነበሩት ብሎ ተገረመ፡፡ ይበልጥ ተሰማው ይበልጥ ሐዘኑን ገለጸ፡፡
ፖሊስም ሕዝብን አከበረ፤ ሠራዊትም ሕዝብን አከበረ፤ ሁሉም ተከባበረ፤ በጋራ አዘነ፡፡
ሁሉም ቦታ ፀጥታና ሰላም ነው፡፡ ሁሉም በሰላም ሥራውን ይሠራል፡፡ ሕዝብ በውስጡ ነገሮችን ለማረጋጋትና ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ በመንግሥት የተወሰደውን ዕርምጃ አደነቀ፡፡ ለካ ሥርዓት ገንብተናል አለ፡፡
ውጭ አገር የሚገኙ አሳዛኝ፣ አሳፋሪና ያልበሰሉ አንዳንድ ተቃዋሚ ተብዬዎችን ወደ ጐን ትተን፣ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ የሚገኙ ተቃዋሚዎችም በሚያስደስት ሁኔታ የተሰማቸው ሐዘን እንጂ ደስታ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ የተበደልን ብንሆንም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በመሞታቸው እናዝናለን እንጂ አንደሰትም አንጨፍርም በማለት ለሟች ቤተሰብና ወዳጆች መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡ ይህም የሚያኮራ ነው፡፡
ለምንድን ነው ይህን ሁሉ እየዘረዘርን ያለነው? ስለዚህስ ጉዳይ ለምን መናገር አስፈለገ? ምክንያት አለ!
ይህ ሁሉ ሕዝብ ሲያዝን፣ ሲያለቅስ፣ ሲሠለፍ፣ ሲጓዝ የሚታየው ቤተሰብና ዘመድ ስለሆነ አይደለም፡፡ የአገር መሪ ስላረፉ ነው፡፡ ለአገር ጥሩ ሠርተዋል ብሎ ስላመነ ነው፡፡ የቤተሰብና የዘመድ ወዳጅ አጀንዳ ሳይሆን የአገር አጀንዳ አድርጐ በመውሰዱ ነው ሕዝብ እንደዚህ ያዘነው፡፡ በፈቃደኝነትና በሙሉ ስሜት ለአገር አጀንዳ ይህን ያህል ክብርና ትኩረት በመስጠቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምስጋናና ክብር ይገባዋል፡፡
ይህ ብቻም አይደለም፡፡ እንደዚህ ሲያዝንና ሲያለቅስ የነበረ ሕዝብ በመንግሥት በኩል ምንም ጉዳት ያልደረሰበት ሕዝብ ነው አይባልም፡፡ ተጠቃሚ ስለሆነ ነው ያለቀሰው አይባልም፡፡ የተበደለም አለ፤ እስር ቤት የነበረና ያለ አለ፡፡ መሬትና ንብረት የተወሰደበትም አለ፤ የተሰቃየ፣ የተሰደበና የተወቀሰም አለ፡፡ ሆኖም ግን የግል አጀንዳንና የአገር አጀንዳን ለያይቶ በማየት እኔ የሚለውን ትቶ እኛ ኢትዮጵያውያንና አገራችን ኢትዮጵያ ብሎ በማዘን ነው የወጣው፤ የተሰለፈው፤ ቦሌ ሄዶ ያለቀሰው፤ ቤተ መንግሥት ገብቶ በእንባ የተራጨው፡፡ የአገርን ጉዳይ ከግል ጉዳይ በላይ አድርጐ ያየ ሕዝብ ነው፡፡
ይህ ብቻም አይደለም፡፡ ቅስቀሳ ስላልተደረገለትም አይደለም፡፡ በየሚዲያው፣ በየኢንተርኔቱ፣ በየፌስቡኩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሞታቸው ዕልል በሉ፣ ተነሱ፣ መንግሥትን ገልብጣችሁ ያዙ የሚል ቅስቀሳ ስላልደረሰውም አይደለም፡፡ ወጣቱ ያውቃል፤ ምሁሩ አውቋል ሰምቷል፤ እንደዚያ የሚሉትን አሳፋሪዎች ናችሁ፤ ከሃዲዎችና የጠላት ተላላኪዎች ናችሁ፤ ገደል ግቡ በማለት አገርን ያስቀደመ ሕዝብ ነው፡፡
ይህን ስላደረገ ነው ይህን ሕዝብ ልናደንቀው፣ ልንኮራበትና ልንመካበት የሚገባን፡፡ ይህን በማድረጉም መንግሥት በግልጽና በማያሻማ መንገድ አመሰግናለሁ ብሎ ለሕዝብ ከበሬታውንና አድናቆቱን መግለጽ ያለበት፡፡ መንግሥት ከሕዝብ ይማር!
በችግር ጊዜ በአንድነት የሚሰባሰብ፣ ከግል ችግር በላይ የአገር ጉዳይን የሚያስቀድም ወርቅ፣ አኩሪና አስመኪ ሕዝብ ነውና ክብርና ምስጋና ለኢትዮጵያ ሕዝብ!