Solving the Diaspora Puzzle: Fostering those in Ethiopia vs. campaigning for others to return

 

በዚህ ርዕስ ልፅፍ ሳስብ በጣም ቆየሁ። ዛሬ ያነሳሳኝ ምክንያት ሁለት ነው። አንደኛው በቅርቡ የሰማሁት በእውነት ላይ የተመረኮዘ ቀልድ ነው። ቀልዶች ወይንም ተረትና ምሳሌዎች ሰምተን ስቀን ወይንም አዝነን ብናልፋቸውም ብዙውን ግዜ ትምህርትና ቅሬታ የሚተላለፍባቸው መንገዶች ናቸው። የተነሳሁበት ቀልድ እንዲህ ነው። አንድ በሙዚቃ ሙያ የሚተዳደር ነዋሪነቱ በሀገር ቤት የሆነ አርቲስት ለእረፍት ወይንም ለስራ ከሄደበት የውጭ አገር ሲመለስ ይዞ የመጣውን ትንሽ ለቤት አገልግሎት የምትሆን የሽንኩርት መፍጫ በቦሌ አየር ማረፊያ ከሚገኘው የጉምሩክ ዴስክ እንዲያስመዘግብና አስፈላጊውን ፎርም እንዲሞላ በቀጭን ትዕዛዝ ቀረጥ እንዲከፍል ይጠየቃል። ይህ አርቲስት በጣም በቀልደኛነትና በቁምነገረኛነት ይታወቃል።

ቅሬታውንም በቀልድ እንዲህ ሲል ይገልፃል “ምነው ምነው ጎበዝ? አከሌና አከሌ ብሎ ሁለት ፈረንጅ አገር ብዙ አመት ኖረው ወደ ሀገራቸው ጠቅልለው የገቡ አርቲስቶች ስም ጠቅሶ “ስንትና ስንት ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የኮንስትራክሽን መኪና ከቀረጥ ነፃ ሲያስገቡ እንዴት እኔን አንዲት ሶስት ራስ ሽንኩርት የምትፈጭ ነገር ትቀርጡኛላችሁ?” ብሎ አለ አሉ። አንድ ቢያጆ ድንጋይ በቅፅበት ዱቄት የሚያረግ መኪና ከቀረጥ ነፃ ሲገባ ሽንኩርት መፍጫ መቅረጥ በርግጥ በጣም የሚያስቅም የሚገርምአጋጣሚ ነው። በወቅቱ ቀልዱን ስሰማም በጣም ስቄያለሁ። ረጋ ብሎ ላሰበው ግን ነገሩ ይከነክናል። የጉምሩክን የአቀራረጥ ሎጂክ ልፅፍበት ሳስብ የነበረ ጉዳይ ነው።

ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ሪፖርተር ጋዜጣ በ ጁን 15 2011 ዕትሙ በርዕሰ አንቀፁ “የዲያስፖራዉን አቅም እየተጠቀምንበት አይደለም የፖሊሲ ለውጥ አሁኑኑ” የሚለው ርዕስ ቀልቤን ስቦት አነበብኩት። ግሩም የሆነ ፅሁፍ ነው። ያሉትን ጋዜጦች በሙሉ ባላነብም ርዕሰ አንቀፆች አያመልጡኝም። ልጅ ሆኜ አባቴ “ጥሩ አንባቢም ሆነ ፀሀፊ መሆን ከፈለክ ሰርክ የምታገኛቸውን ጋዜጦች ርዕሰ አንቀፃቸውን አንብብ” ይለኝ ነበር በተለይ የእንግሊዘኛ ህትመቶችን። ርዕሰአንቀፅ (Editorial) በውስን ቃላት ትልልቅ ርዕሶች የሚዳሰስበት አምድ ፤የፀሀፊዎችንም ጥንካሬና የአፃፃፍ ክህሎት የሚለካበትና የሚታይበት እንደሆነ ተረድቻለሁ።ግዜ ሳገኝ የአማርኛም ሆነ የእንግሊዘኛ ህትመቶች ርዕሰ አንቀፃቸውን ሳላነብ አልውልም።በኒዮርክ ታይምስና ዎሽንግተን ፖስት ብቻ አልወሰንም የአማርኛ ህትመቶች ቀልቤን ይስቡታል።

በጠቀስኩት የሪፖርተር ርዕሰ አንቀፅ የሰፈረው ነገር በሀሳቡ መነሻና መድረሻ እየተስማማሁ አንዲት ነገር ለማከል እፈልጋለሁ።

ግልፅና አሻሚ ያልሆነ ፖሊሲ ለማንም ለምንም አስፈላጊ ነው፤ አቅም የሌለውን አቅም እንዲገነባ የሚደግፍ ፖሊሲ መቅረፅ ደግሞ ዘላቂ ሀገራዊ ዕድገት ማረጋገጫ ነው። ህብረተሰቡን በየእርከኑ መድረስ ከተቻለ ትኩሳቱንም ለክቶ ፈውስ መዘየድ በቀላሉ ይቻላል። የትኩረቱ ቅድሚያ ግን በእጅ የያዙት ላይ ነው ማመዘን ያለበት !

በሀገር ቤት ነዎሪ የሆነውን ህብረተሰብ ሳይደግፉ ለዳያስፖራው ብቻ አልጋ በአልጋ የሆነ ህግ መውጣት የለበትም ብዬ አምናለሁ። ባለፉት ሁለት አስርተ አመታት ለዳያስፖርው የሚደረገው ማበረታታት ሲግልም ሲቀዘቅዝም አይቻለሁ። ለረጅም አመታት በተለያየ መንገድ ከሀገሩ ርቆ የቆየ ዜጋ ወደ እናት ሀገሩ ጠቅልሎ ለመመለስ ሲነሳ ጥቂት ጥሪት ይዞ መሆኑ የማይታበል ሀቅ ነው። የተቃረመው ዕውቀትም ሆነ ንብረት ለሀገር እድገት ወሳኝ ነው። የስምሪቱም ዘርፍ እንደ የጥቅም ደረጃው ይለያያል። ሊበረታቱ የሚገባቸው መስኮች አፍሪካን ለመሳሰሉ ሀገራት ተመሳሳይነት አላቸው። የሚቀረፁት ፖሊሲዎች ሀገሪትዋያላትን ክፍተት የሚሞሉ እስከሆነ ድረስ የማበረታቻው ድጎማ በየፈርጁ መለያየት ይኖርበታል።

ኢትዮጵያ መቼም የውስኪ ቤትና የመብል ቤት እጥረት አለባት ብዬ ባልገምትም እርሻ፤ኮንስትራክሽን፤የሳይንስናቴክኖሎጂ ፤የህክምና፤የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች እጥረት ይኖራል ብዬ እገምታለሁ።በሀገር በቀል ነጋዴዎች የሚሰሩና ሊሰሩ የሚችሉትን ስራዎች ከፍተኛ አቅም ባላቸው ነጋዴዎች እንዳይዋጡ ተገቢውን ህጋዊ መከላከያ መስጠት ያስፈልጋል።ከውጭ ትልቅ አቅም ይዘው ያለውን የታክስ ጥቅም ደርበው ሀገር በቀል የሆኑ ትንንሽ አቅም ያላቸው ድርጅቶች ውድድሩን ስለማይችሉት ከጨዋታ ውጭ የሚሆኑበት ሁናቴ ይፈጥራል። አንድ ወጥ የሆነ የዳያስፖራ ፖሊሲ ጠቃሚነት የለውም ጉዳት ሊኖረው ግን ይችላል።

ዛሬ ዋና ላስጨብጥ የተነሳሁት የታክስ ቅነሳና የተሻለ እንክብካቤ የሚያስፈልገው ሀገሩን ጥሎ ሳይወጣ እዛው ከሰፊው የሀገሩ ህዝብ ጋር ለሚታገለውና ለሚሰራው ባለሙያ ነው የሚል አስተሳሰቤን ነው(በተለይ መምህራኖችን) ምክንያቴን መዝጊያዬ ላይ አስረዋለሁ።፡በተለያዩ ሀገሮች መምህራን፤ወታደሮች፤ሀኪሞች በብዙ ረገድ ድጋፍ ያገኛሉ ለምሳሌ የቤት መስሪያ ልዩ የብድር አገልግሎት፤በቅናሽ የምግብ አቅርቦት

የሚገዙበ ፤ የመሳሰሉ ድጎማዎች።፡ ሀገሪትዋ ቁልፍ በምትላቸው የሙያ ዘርፍ ለተሰማሩ ዜጎች እንደየአስፈላጊነታቸውና ክፍተት ባላቸው ዘርፎች ድጋፍ ይሰጣል።

አንድ ቀለል ያለ ምሳሌ ብንወስድ ሁለት ወደ አውሮፓ ለትምህርት የሄዱ ኢትዮጵያዉያን ትምህርታችውን ሲጨርሱ አንደኛው ወዲያው ወደ ትውልድ ሀገሩ ተመልሶ በአንድ ዩኒቨርስቲ ማስተማር ቢጀምር፤ ሌላኛው ደግሞ ከሄደበት ቀርቶ ከተወሰኑ አመታት በሁዋላ ወደ ሀገሩ መመለስ ቢወስን ከላይ የጠቀስኩት አይነት መደጎሚያዎች መኪናና የቤት እቃ ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገባ ይፈቀድለታል። የውጭ ምንዛሪም ቆጥቦ ከበቂ በላይ ሊይዝ ይችላል።

በአንፃሩም ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ሳይውል ሳያድር ወደ ትውልድ ሀገሩ ገብቶ አስር አመት ሙሉ ወገኑንና ሀገሩን ሲታደግ የቆየው ዜጋ ጫማው እስኪጣመም በፀሀይና በውርጭ ላይ ደፋ ቀና ሲል ቆይቶ ከእጅ ወደ አፍ በሆነች ደሞዙ ሲውተረተር ይታያል። እንደኔ እንደኔ ቢሆን ተመጣጣኝና አግባብነት ያለው የታክስ ስርአት ተቀርፆ በዚህ መስመር የሚሰበሰበው ታክስ የተወሰነው ፐርሰንት ሀገራቸውን ትተው ሳይፈልሱ ቁልፍ ቁልፍ በሆኑና በተመረጡ ሙያዎች ላይ ለሚሳተፎ ዜጎችን በቂ ደሞዝ መክፈያ ብሎም መደጎሚያ፤በተሰለፉበት ሙያ ቢያንስ ሻል ባሉ የአፍሪካ አገሮች መመዘኛ ቤት መስሪያ፤መኪና መግዣ ማግኘት አለባቸው ብዬ አምናለሁ።በየግዜው የምናየውንም የተማረ ሀይል ፍልሰትንም ሊቀንሰው ይችላል።ዳያስፖራን ብቻ እንደ በኩር ልጅ ማባበል ሳይሆን በሀገር ቤት ያለውን ባለሙያ መንከባከብ በጣም አስፈላጊ ነው።፡

ማንኛውም ዜጋ በሰለጠነበት ሙያ ሀገሩንና ህዝቡን የመታደግ ሀለፊነት አለበት። ከትውልድ ወደ ትውልድም እውቀትና እድገት ሊተላለፍ የሚችለው ጥሩ አስተማሪና ተማሪ ሲኖር ነው። መምህርነት በየትኛውም የአለማችን ማዕዘን የተከበረ ሙያ ነው። የነገውን ትውልድ አንፆ የሚያዘጋጅና በዲሞክራሲ የሚኖርን ህብረተሰብ ዕጣ ፈንታም ወሳኝ ነው። በዚህ ሙያ የተሰለፉት ወገኖቻችን ተተኪው ዜጋ በዚህ ሙያ እንዲሰለፍ አርአያ መሆንና ለተማሪዎቻቸው ተስፋ መፈንጠቅ መቻል አለባቸው። በአቅም የተቸገረ ተክለ ሰውነቱና በመንፈስ የተረበሸ፤ ገፁ ችግሩን የሚተርክበት መምህር የሚያስተላልፈው ዕውቀት

ተቀባይነቱ አጠራጣሪ ነው ምክንያቱም እውቀቱ ቢያንስ እራሱን/ዋን ማሸነፍ አላስቻለምና ነው። በግልና በመንግስት ትምህርት ቤት ያሉትን መምህራን የኑሮ ልዩነት ማየት ይበቃል። በተሰለፉበት ሙያ አድሎአዊና ፍትሀዊ ያልሆነ የህግ ስርዓት ሲኖር ልክ እንደሌሎች ባልንጀሮቻቸው አስርም አስራአምስት አመትን መሰደድ ይመርጣሉ። ዛሬ በርካታ ዩኒቨርስቲዎች በአራቱም ማዕዘናት ቢገነቡም የትምህርት ጥራቱ አጠያያቂ ነው። ባለው የመምህራን እጥረትም ከናይጄሪያና ከሌሎች አገሮች ክፍተት ሊሞላ እየመጣ ያለውን የሀገራችንን የውጭ ምንዛሪ ሽሚያ ውስጥ ይገባል። ያለውም የክፍያ ልዩነት የዜጎችን ሞራል ይነካል።

የአንድን ሀገር ህብረተሰብ ሞራሉ እንዲገነባና ራስ ቀና ተደርጎ እንዲኬድ ለሀገር ቤት ነዎሪው ቅድሚያና እንክብካቤ መደረግ ይገባዎል። ዳያስፖራው በቀረጥ ነፃ ባስገባው መኪና የሚያንፉዋልልበት መንገድ ሀገሩን ጥሎ ሳይሰደድ ታክስ በከፈለው ዜጋ ላብ መሆኑ መዘንጋት የለበትም። መሰደድና ውጭ ከርሞ መምጣት የተሻለ እውቀትና አቅም ይዞ መመለስ ከሆነ ከሌላው ዜጋ የተለየ አልጋ በአልጋ የሆነ ፖሊሲ መንደፍ አይጠይቅም። አልጋው ተዘርግቶ ከተነጠፈ ቀደም ብሎ አረፍ ማለት ያለበት ታክስ ከፋዩና በሀገር ቤት የሚገኙት ዜጎች ናቸው።

ቸር ይግጠመን : ሳምሶን ደምሴ ተፈራ::

Categories: 

Related Posts

About author

admin's picture

Asratie's picture
Asratie (not verified) Mon, 10/01/2012 - 10:12

Selam Samson,

Thank you for your article above on the Diaspora policy. You nailed it down right, and I hope the policy makers and those of us in the Diaspora make a note of it. Thank you for your insight.

Asratie,

Samson's picture
Samson (not verified) Wed, 10/03/2012 - 21:58

I hope so my brother. Thanks for the comment. I wish more people weigh in on the topic. I was just sharing my two cents worth,,,,

Post new comment

Plain text

  • No HTML tags allowed.
  • Web page addresses and e-mail addresses turn into links automatically.
  • Lines and paragraphs break automatically.